አዕማደ እምነት | Statement of Faith

አዕማደ እምነት / Statement of Faith/

ክራይስት ዲሳይፕልስ ሚሽን ዩኒቨርሲቲ እንደ አንድ ስነ መለኮት ትምህርት ተቋም የሚከተሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮአዊ እውነቶችን ያምናል።

1. መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት ቃል መሆኑን እና የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ ያሉትን ቃላት በእግዚአብሄር ልብ እንዳሉ መጻፋቸውን እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያዎቹ የእጅ ጽሑፎች ምንም ስህተት የለለበት በሰው ቋንቋ የተጻፈ መለኮታዊ መጽሐፍ ነው። በዘመናት መካከል ከተቃጣበት ጥቃት እግዚአብሔር በመለኮታዊ ኀይሉ መጽሐፍ ቅዱስን ጠብቋል ብለን እናምናለን።

2. ሥላሴ

በሦስት የተለያዩ አካላት (አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) ተገልጾ ለዘላለም በሚኖር በአንድ እውነተኛ አምላክ እናምናለን፡፡ እነዚህ ሦስቱ አካላት ፍጹም ሙሉአዊና እኩል እግዚአብሔር ሲሆኑ፣ ሁሉም እኩል የሆኑ መለኮታዊ ባሕርይ ያላቸው እንዲሁም በእኩል ደረጃ ናቸው። አብ ወልድ አይደለም፤ ወልድም አብ አይደለም። አብ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስም አብ አይደለም። ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስም ወልድ አይደለም። እግዚአብሔር አብ የሥላሴ የመጀመሪያ አካል፣ ዘላለማዊ፣ የማይለወጥ፣ ሁሉን የሚችል፣ ሁሉን የሚያውቅ፣ በጥበብ የላቀ፣ ሁሉን የሚወድ፣ ፍጹም ጻድቅና ፍጹም ቅዱስ፣ ሉዓላዊ ገዢና ፍጥረተ ዓለምን በእጁ የያዘ መሆኑን እናምናለን፡፡

እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ የሥላሴ ሁለተኛ አካል መሆኑን እንዲሁም እግዚአብሔ ርን ለሰው ልጆች ሊገልጥ፣ ትንቢትን ሊፈጽም፣ የጠፋውን ዓለምንም ሊያድን ሥጋን የለበሰ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አንድያ ልጅ መሆኑን እናምናለን፡፡ ኢየሱስ ሰው ሲሆን አምላክነቱን በምንም ሁኔታ አልተወም፤ ስለዚህ እርሱ ለዘላለም በአንድ አካል ውስጥ የማይነጣጠልን ባሕርይ በመያዝ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ኢየሱስ በተአምራት በመንፈስ ቅዱስ ተጸነሰ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ ያለ ምንም ኀጢአት ኖረ፤ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ለሚሠሩት ኀጢአት ሁሉ ፍጹም በቂ የማስተሰሪያ መሥዋዕት በመሆን በምትክነት በመስቀል ላይ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በአካለ ሥጋ ከሙታን ተነሣ፤ በከበረውና ከሙታን በተነሳው አካሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ ዐረገ፤ የምልጃ አገልግሎቱን በመፈጸም በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል፤ ሙሽሪትን ቤተ ክርስቲያን በአየር ለመቀበል ደግሞ ይመለሳል።

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ ሦስተኛ አካል መሆኑን ክርስቶስን ለማክበርና በክርስቶስ የተገኘውን ድነት ሰዎች መቀበል እንዲችሉ ለማድረግ በተለይም በበዓለ ሃምሳ ቀን ደቀ መዛሙርት ላይ እንደወረደ እናምናለን፡፡ ዓለምን ስለ ኀጢአት በመውቀስ ሰዎች ዳግም ልደትን እንዲያገኙ የሚረዳ እሱ ነው፡፡ ከድነት ጋር አብሮ መንፈስ ቅዱስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣል! በዘላቂነት በእኛ በአማኞች ውስጥ ያድራል፤ እስከ ቤዛ ቀን ድረስም የአማኝ ዋስትና መያዣ በመሆን ያትመዋል:: መንፈስ ቅዱስ ራሳቸውን የሰጡትን አማኞች ይሞላቸዋል ማለትም ይመራቸዋል፤ ይቆጣጠራቸዋልም፤ አማኞች ፍሬ እንዲያፈሩ ያደርጋቸዋል።

3. ሰው

ሰው በእግዚአብሔር መልክ በራሱ በእግዚአብሔር እጅ እንደተፈጠረ እንጂ ፈጽሞ በዝግመተ ለውጥ ሂደት እንዳልመጣ እናምናለን። ሰው የተፈጠረው እግዚአብሔርን ሊያከብር፣ ሊያመልክ፣ ሊያገለግል እንዲሁም ከእርሱ ጋር ኀብረት ሊያደርግ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ በኀጢአት ወደቀ፤ ይህም መንፈሳዊ ሞትን በማስከተል ከእግዚአብሔር ለየው፡፡  የሰው ተፈጥሮ በመበላሸቱ ማለትም «በኀጢአትና በበደል ሙት» በመሆኑ በመሉ ጠፋ፣ ራሱን ለማዳን እንዲሁም ተመልሶ በራሱ ሥራ ወይም ጥረት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማስተካከል ወደማይችልበት ደረጃ ደረሰ።

በሰው ሁለንተና እናምናለን። ሰው መንፈሳዊ እንጂ መንፈስ አይደለም! በሰው ሁለንተና እናምናለን ስንል ሰው መንፈስ፣ ነፍስ እና ስጋ አለው ማለታችን ነው። ይህ ሁለንተና በቅድስና ያለ ነቀፋ መጠበቅ እንዳለበት እናምናለን። (1ኛ ተሰ 5፡23 ፤ 2 ቆሮ 7፡1)

4. ሰይጣን

ሰይጣን የክፋት አነሳሽና በተጨባጭ ያለ መንፈስ ነው። እርሱ የወደቀ መልአክ ሲሆን፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ የምድር ገዥ እንዲሆን ጊዜያዊ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ሰይጣን በመስቀል ላይ ሙሉ በሙሉ ተሸንፎአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የሚፈጽመው ፍርድ ከሺሁ ዓመት መንግሥት በኋላ ለዘላለም በእሳት ባሕር አስከሚጣልበት ጊዜ ድረስ ተላልፎአል፡፡ እኛ አማኞች በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመደገፍ ልንቃወመው እንድንችል ሥልጣን አለን።

5. ድነት

ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነትና ጌትነት እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የመስዋዕትነት ስራ ሲያምን የእግዚአብሔር ጸጋ ነጻ ስጦታ የሆነውን የኀጢአት ይቅርታንና ድነትን ያገኛል። ድነት በሰው ሥራ ወይም የግል ብቃት ፈጽሞ አይገኝም:: ድነት የሚገኘው አንድ ሰው ክርስቶስ በፈጸመው ሥራ ላይ እምነቱን ሲያደርግ ብቻ ነው:: ንስሐ መግባት ወደ እግዚአብሔር ዘወር ማለትና ከኀጢአት መራቅ ሲሆን ለድነት የሚያበቃው እምነት ክፍል እንጂ የተለየ አይደለም:: በእምነት ኢየሱስ ክርስቶስን የሚቀበሉ ዳግም ይወለዳሉ፤ ኃጢአታቸው ይቅር ይባልላቸዋል ፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፤ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ናቸው።

6. የክርስትና ሕይወት

ማንኛውም ክርስቲያን ለራሱ ሳይሆን ለክርስቶስ መኖር እንዳለበት እንዲሁም በውስጡ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ኀይል ለእግዚአብሔር ክብር ክርስቶስ የራሱን ሕይወት በእርሱ ውስጥ እንዲገልጥ መፍቀድ እንዳለበት እናምናለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል አብዝቶ በመታዘዝ እያንዳንዱ አማኝ መብሰልና ክርስቶስን ወደመምሰል መድረስ አለበት እንጅ የሥጋን ምኞት መፈጸም የለበትም፤ የክርስቶስን አካል ለመገንባት መንፈሳዊ ስጦታዎቹን መለማመድ ይገባዋል፤ የክርስቶስ ምስክር መሆን አለበት፤ ታላቁን ተልእኮ ለመፈጸም በግሉ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ሥራ ውስጥ መሳተፍ ይኖርበታል፤ ለእግዚአብሔር ክብር ይሆን ዘንድ መልካም ሥራን መሥራትና ፍሬን ማፍራት አለበት።

ክርስትያናው ጋብቻን በተመለከት ጋብቻ ክቡር የሆነ የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት የእርሱ ተቋም ነው። ጋብቻ የሚፈጸመው በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ እንደሆነ እናምናለን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን የጾታ፣ የስርአተ-ጾታ  እና የጋብቻ ትርጉም እንቃወማለን።

7. ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል፣ ክርስቶስም ራስዋ እንዲሁም አባሎችዋ ክርስቶስን በእምነት በእውነት የተቀበሉ መሆን እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ አንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በተወሰነ ስፍራ የክርስቶስ አካል ተጨባጭ መገለጫ ናት፡፡ በክርስቶስ አካል ያሉ አማኞች በሙሉ በአንድ መንፈስ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስለሆኑ በፍቅር፤ በስምምነትና በአንድነት መኖር አለባቸው። በተለያዩ የወንጌል አማኝ ቤተ እምነቶች ቀና በሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ላይ የተመሰረተ ልዩ ልምምድ ቢኖርም ተመሳሳይ ዐላማ ካለ፤ ቋሚ ካልሆነ አስተምህሮአዊ ጉዳይ ጋር ያልተገናኘ ነገር በአገልግሎት መለያየት ወይም እገዳን የሚያስከትል መሆን የለበትም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዐላማ ክርስቶስን ለጠፉት ማስተዋወቅ፣ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት፣ በምድር ላይ እግዚአብሔርን ማክበር ነው::

8. በጌታ የተሰጡ ሥርዓቶች

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡንና በቤተ ክርስቲያን የታወቁ ሁለት ሥርዐቶች የውሃ ጥምቀትና የጌታ እራት ብቻ እንደሆኑ እናምናለን፡፡ የውሃ ጥምቀት ተጠማቂውን ውሃ ውስጥ በማጥለቅ የሚፈጸም ሲሆን፣ ከድነት በኋላ የሚፈጸም ትእዛዝ ነው፤ ይህም በምሳሌነት የሚያመለክተው የአማኙን ለኀጢአት መሞት፣ የአሮጌውን ሕይወት መቀበርና የአዲሱን ሕይወት ትንሣኤ ነው፡፡ የጌታ እራት ከክርስቶስ ጋር ያለንን ኀብረትና አንድነት የምንገልጥበት ሲሆን፣ ሞቱንና ዳግመኛ መምጣቱን በማሰብ የሚፈጸም ምሳሌያዊ መታሰቢያ ነው። (ማቴ 28፡19፣ ሉቃ 22፡19-20፣ 1ቆሮ 11፡23-26፣ የሐዋ.ሥ 10፡47-48)

9. የሰዎች የዘላለም እጣ ፈንታ

እያንዳንዱ አማኝ ሲሞት ነፍሱ እያወቀች ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ጋር ሕብረት ወደሚደረግበት ወደ ሀልዎቱ በመግባት ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ የአካል ትንሣኤንና የሥጋውን ክብር ለመቀበል በዚያው እንደሚጠባበቅ እናምናለን፡፡ ስለዚህ አማኝ ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ሕይወትን ይኖራል፤ ይኸውም ለዘላለም ከእርሱ ጋር ለዘላለም ሕብረት እያደረገና እያመለከ የሚኖረው ኑሮ ነው። ያላመነ ሰው ሲሞት ነፍሱ እያወቀች ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ወደሚኖርበት ሁኔታ በመግባት አካለ ሥጋው ተነሥቶ የዘላለም እርግማን፣ ፍርድና ቅጣት የሚቀበልበትን ቀን እንደሚጠባበቅ እናምናለን።

10. የወደፊት ነገሮች

የሚቀጥለው ትንቢታዊ ሁነት ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ያሉትን አማኞች ሁሉ በአየር ወደ ራሱ የሚቀበልበት የቤተ ክርስቲያን ንጥቀት እንደሆነ እናምናለን ከቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ቀጥሎ የዳን. 9:24-27 ትንቢት ፍጻሜ የሆነውና በራ. 6፡1 - 19:21 የተዘረዘረው የሰባቱ ዓመት የታላቁ መከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚህ ዘመን እስራኤል ነጥራ ትወጣለች ፤ መላው ዓለም ይፈተናል፤ የእግዚአብሔርም ቁጣ በኀጢአት ላይ ይወርዳል (ዳን. 30:7፤ ማቴ. 24 ራዕ. 3:10 1ተሰ. 5:9-11)::

በታላቁ መከራ ማብቂያ ላይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ በታላቅ ኀይልና ክብር እንዳረገው ሁሉ ዐይን ሁሉ እያየ በአካል የሺህ ዓመት ዘመን አገዛዝ ይዞ ወደ ምድር ይመለሳል (ራእ. 19:11-21 የሐዋ.ሥ 1:8-11)። ክርስቶስ በምድር ላይ ሺህ ዓመት ከገዛ በኋላ የሚቀጥለው ዘመን በሰይጣን ላይ የሚፈጸመው የመጨረሻው ፍርድ ነው፤ በዚህ ጊዜም ሰይጣን ለዘላለም ወደ እሳት ባሕር እንደሚጣል፣ ታላቁ የነጭ ዙፋን ፍርድና ያላመኑ ሙታን በአካል እንደሚነሡ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚፈጠሩ፣ የዘላለም መንግሥት እንደሚሆንም እናምናለን (ራእ. 20 - 22፤ 2ጴጥ. 3:1-14)::